Monday 10 March 2014

አድዋ



Emperor Menelik
Empress Taitu
አድዋ
02/03/14 ከመራሹ






ሞፈሩን ቀምበሩን ምሰሶ አስደግፎ
የሃገሩን ፍቅር በልቦናው አቅፎ
ከምኒሊክ ጦር ጋር ጀግናው ተሰልፎ
ምሽትና ልጆቹን ጣፋጯ ጎጆውን
ወደኋላው ትቶ ቋጠረና ስንቁን
ወድሮ ጦሩን አንግቦ ጋሻውን
አሳዶ ሊቀጣ ጣሊያን ወራሪውን
እመር እመር አለው ጋራ ሸንተረሩን
ባዶ እግሩም ደፈረው ቋጥኝ አረንቋውን
ንዳድ በረሃውን
ብርድና ቁርፋዱን
ተቋቁሞ ወጥቶ ሊደቁስ ጠላቱን።
ኦ !! እናት ሃገሬ የነፃነትና የፍትህ መረዋ
ደሙንም አፍሦ አጥንቱን ከስክሶ ላንቺ የተሰዋ
በታሪክ መኩሪያችን በድል አምባ አድዋ
ለቅኝ ገዥዎች የሽንፈትን ፅዋ
በጥብጦ የጋተው ምኒልክ እምዋ
ስንኩል ስራቸውን ግብዓቱን ፈፅሞ
በታሪክ መዛግብት ተከትቦ ታትሞ
ሲወሳ ይኖራል ዛሬም ዘወትርም
ተምሳሌው ላፍሪካ ተምሳሌው ለዓለም።
Ras Mekonnen
ሐገር ብቻ ሳይሆን ጦሩንም የመራ
እምዬ ምኒሊክ አሞተ ኮስታራ
የጦር መሪም ሆኖ አዛኝ እንደ እናቱ
ውሳኔን ከቴዎድሮስ መላን ከጣይቱ
አጣምሮ አዋሕዶ ለድል ያደረሳት
እምዬ ምኒሊክ ከወራሪ ፋሽስት ከሶላቶ አዳናት።
ኦ !! እናት ሃገሬ የነፃነት ደወል የፍትህ መረዋ
ከአፅናፍ እስከአፅናፍ ተዛምቶ ዝናዋ
በታሪክ ክስተቱ በመኩሪያዋ አድዋ
ቅኝ ገዢን ሁሉ ተስፋ ያስቆረጠ
ጭራን አስቆልፎ ዱር ያስፈረጠጠ
የነፃነት ብርሃን ድል ያስቆነጠጠ
የምኒልክ ሐገር በኩራት ናጠጠ።
መጀመሩን ፈርቶ ከምሽግ አድብቶ
Dejazmach Balcha
ምን ይልክ እያለ ሲጨነቅ ሶላቶ
ጦሩ ሲቁነጠነጥ ከውጊያ ዘግይቶ
እራሱ መጣበት እየበላ አንኩቶ
ጭለማው ደቅድቆ እረዝሞ ለሊቱ
ሰማይ ተገለጠ ብቅ አለች ጣይቱ
ምንጩን አደረቀች ዘጋች ከብልቱ
እጃቸውን ሰጡ በውሃ ጥማቱ
እንግዲህ ፈረንጆች ምንም ቢዶልቱ
አልቀረላቸውም ውርደቱ ሽንፈቱ
ላንዴም ለሁለዜም ተሰነባበቱ
አልገዙም አገሬን እንደተመኙቱ።
ዘመን ተቆጠረ ይህ በእንዲህ አልፈ
ክብረ በዓል ሆኖ ጀግና ተሰለፈ
ግጥም ተነበበ ቅኔም ተዘረፈ
የጀግና ደርት ላይ ሜዳል ተለጠፈ።

ግና መች አበቃ ቂመኛው ሶላቶ
አርባ አመት ተኝቶ አርባ አመት አስልቶ
እንደገና መጣ ጦሩን አደራጅቶ
ጥይት አበራክቶ የጭስ መርዝ ሰርቶ

Ras Mengesha
በመድፍ በአውሮፕላን በባንዳ ተመርቶ።
ኦ !! እናት ሀገሬ ጀመረ ስቃይዋ
ተሰራጨ ውስጧ በመላ ገላዋ
በቅኝ ገዥዎች ሊፈተን ጤናዋ
በነገስታት ዘመን ጣልያን ያልተኛላት
አምስት ዓመት ሙሉ ከረመ ሲወጋት።
ጀግናው በየፈፋው ጀግናው በየጫካው
ጀግናው በከተማ ባደባባይ ጀግናው
የጣልያንን አንገት በካራ ሲቀላው
አምስት ዓመት ሙሉ መቀመጫ አሳጣው።
ያድዋው ድል ታሪክ ድጋሜ ተሰርቶ
በእነ አባ ገስጥ አቤ አንገቱ ተቀልቶ
ካገራችን ወጣ ወራሪው ሶላቶ።
ኢትዮጵያ ሃገሬን መግዛት አቅቷቸው
ድጋሜ ሽንፈቱ ያልተዋጠላቸው
አልጠፋም እስካሁን ቁስል ጠባሳቸው
እድሜልክ ይኖራል ሲመዘምዛቸው ።
ያቆረዘዘው ቂም ዘንድሮ ገንፍሎ
በጣሊያን አፊሊ (Affile) ትዝታው አብቅሎ
ለፋሽስቱ ግራዚያኒ ሐውልት ተተክሎ
በጦር ያጡትን ድል በአእምሮ ሊተኩት
ሕዝብን ለፈጀ ስው ሐውልት ሰሩለት።
Ras Alula
ሐበሻው ተናጠ
ተቃውሞው ቀለጠ
ምነው መንግስታችን ክፉኛ አለመጠ ?
ተቃውሞ የወጣን ወጣትና አዛውንት
በሽመል ቀጥቅጦ ዘብጥያ ማስገባት
ምን በደለ ሐበሻ ጥፋቱ የፋሽስት
ሕዝብን ለፈጀ ስው ሐውልት የሰራለት።
እንደው ለመሆኑ ምንድን ቸገራቸው ?
በሐገር ሲላገጥ ዝም ማለታቸው
ለጣሊያን ሶላቶ መድረክ መልቀቃቸው
የድሮው ባንዳነት አገረሸባቸው ?
ወይንስ ሊሬ ገባ በከረጢታቸው
ልጓም የሚጎትት ቶሽ እሚል የላቸው
እንደ ዱር አጋሰስ መረን መውጣታቸው።
     ኦ !! እናት ሃገሬ የነፃነት ደወል የፍትህ መረዋ
     ደሙንም አፍሦ አጥንቱን ከስክሶ ላንቺ ለተሰዋ
     ለታሪክ መኩሪያችን ለድል አምባ አድዋ
     ክብር እንሰጣለን
     ለወደቁ አባቶች እንፀልያለን
     መታሰቢያ ሐውልት በወርቅ እንቀርፃለን
በእምዬ ምኒልክ ስም እንሰይማለን
ያራዳው ጊዮርጊስን
ፒያሳ ከተማውን
እንጦጦ ጋራውን

ምኒልክ ጦር ሰፈር ምኒሊክ ከተማ የምኒልክ ጋራ እናሰኘዋልን።

No comments:

Post a Comment