Saturday 23 March 2024

ለአድዋ ድል ማርያማዊ መርሆ ነው፡፡

 የፈራረሱት ስርአታት

መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ/ም

ቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com

ለአድዋ ድል ማርያማዊ መርሆ ነው፡

ስለ አድዋው መታሰቢያ የሚሰማህን አካፍለን ብሎ አንድ ሰው ጠይቆኝ ብጽሑፍ አዘጋጂቼ ሳለ በቦታው ተገኜቼ ያዘጋጀሁትን ለማቅረብ ስላልተመቼኝ አላቀረብኩትም ነበር፡፡

ያዘጋጀሁት ጽሑፍ በእለቱ ለማቅረብ ባልችልም ይጠቅማል ብየ ስላሰብኩ ላንባቢ ይደርስ ዘንድ ለድረገጾች ለመላክ ስዘጋጅ ከድሉ በዐል ጋራ ተያይዘው ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸው ስብሰባወች በተከታታዩ ተካሄዱ፡፡

1ኛ:-128ኛውን የአድዋው የመተሳቢያ በዐል የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ/ም የተደረገ ስብሰባ
2ኛ:-የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ/ም የታወሰውን የፓትርያርኩ 11ኛ በዐለ ሲመት፡
3ኛ: ካህናት የመሰሉ ጥቂት ሰዎች የነበሩበት መጋቢት 7 ቀን 2016 የተደረገው ስብሰባ
4ኛ:- በጠቅላይ ምንስቴሩ መሪነት ፓትርያርካችን የተገኙበት ስብሰባ
5ኛ፦የፕሮቴስታንቶች ስብሰብ
6ኛ፦የሙስሊም ወገኖቻችን ስብሰባ

ባለፉት ሳምንታት በተከታታይ የተካሄዱትን ሰብሰባወችን ሁሉ ቃኘኋቸው፡፡

እንዳግጣሚ የዘመናችን ምሑራን ስለ ሀገር በሚነጋገሩበት አውድ ላይ “Quantum physics and the Quest for the Elusive National Dialogue in Ethiopia” በሚል በአቶ ጸሐይ ደመቀ የቀረበውንም ተመለከትኩ፡፡

ከአድዋው የመተሳቢያ በዐል ጀምሮ እስከ ሙስሊም ወገኖቻችን በተከታታይ በጠቅላዩ እየተቃኙ የተደረጉትን ስብሰባወች ስመለከት ከአድዋው ድል ያልራቁ ተሰናስለው የቀጠሉ መሰለኝና ኬንያ Embuu በሚባለው ቦታ St Andru College በነበርከበት ጊዜ የ Anthropology እና የsosiology ትምህርት መምህሮቻችን ይጠቀሙባቸው የነበሩት ዘዴወች ትዝ አሉኝ፡፡

ተማሪወች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመጣሁት በቀር የቀሩት ሁሉም እንግሊዝ በቅኝ ትገዛቸው ከነበሩት በኋላ በኮመንዌልዝ ከተሳሰሩት አገሮች እየተመረጡ የመጡ ናቸው፡፡ መምህራኑ እንግሊዞች ናቸው፡፡ ተማሪወችን በቡድን ከፍለው በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ወንጌል ስበኩ ብለው በየደረስንበት የሚገጥመንን እንድንጽፍ ደብተርና በእር አሲዘው ይበትኑናል፡፡

መምህራኑ የጻፍነውን ይሰበስቡና “epilog” የሚል ሰአት ተዘጋጅቶለት እየተነበበ ይተቻል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋል እያንዳንዱ ተማሪ ቢያንስ በአንድ ገጽ የተጠቃለለ የራሱን ሀሳብ እንዲጽፍ ይገደዳል፡፡ ሁሉት ጥቅም ይኖረዋል፡፡ አንደኛው መምህራኑ ከቤታቸው ሳይወጡ ተማሪወች ለፍተው በሚያቀርቡት አማካይነት የሕብረተ ሰቡን ሁኔታ አዳዲስ ሐሳብ ይማሩበታል፡፡ የነበራቸውን እውቀት ያጠነክራሉ ያድሳሉ፡፡ ምክንያቱን ለወንጌል ስብከት ይበሉት እንጅ ዘግይቼ እንደተረዳሁት ህብረተ ሰቡን ለማጥናት ነበር፡፡

ይህ ዘዴ በባእድ አገርና ቋንቋ ስለገጠመኝ እንጅ በቅኔ ትምህርት ቤት ሳለሁ ሳደርገው ከነበረው የተለየ አልነበረም፡፡ የቅኔው መምህር ለተማሪወቻቸው አቅጣጫ ጠቋሚ (sample) አዲስ ቅኔ ለተማሪወቻቸው ይዘርፋሉ፡፡ የዘረፉትን ቅኔ ይዘቱን ቅርጹን ከቀጸልን በኋላ ወደ ሕብረተ ሰቡ በመሄድ በየጫካውም በመበትን የየራሳችን ቅኔ በመቀመር ባንዲት ነገር ላይ የማይመሳሰል ሐሳብ ይዘን እንቀርባለን፡፡ መምህሩ ተማሪወች ከህብረተ ሰቡ ባየትና በሰሙት ላይ መስርተው ቆጥረው ቢሚያቀርቡላቸው ቅኔወች አዳዲሲ ነገሮችን ይማሩባቸዋል፡፡ በሚቀጥለው አፍሰው ለሚዘርፉት ቅኔ የታመቀ ሀሳብ ያገኙበታል፡፡

ጠቅላዩ በዚህ ሳምንታት ውስጥ በተከታታይ የመሯቸው ስብሰባወች በቅኔ ትምህርት ቤትና በኮሌጅ ሳለሁ ሳደርጋቸው ከነበሩት ልምዶች ጋራ ተመሳሳይ ሆነው አገኘኋቸው፡፡

ጠቅላዩ አገር ሲመሩበት የነበረው ፈሊጥ አርጅቶባቸው ሊወድቅ አፋፍ ላይ ሲደርስ ለማፍረስ የፈለጉትን ለማፍረስ ለመገንባት የፈለጉትን ለመገንባት ኃይላቸውንና አቅማቸውን በአዲስ ዘዴ አጥናክረው ለመቀጠል የተማሩበት መሰለኝ፡፡

የአድዋውን ድል መርሆ ያዘጋጀችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን በመምራት ያሉትን የተረዳሁት እየተጎተቱ ሄደው ሲኖዶስ የሚባለውን አንቀው ገለው ከዓቢይ ጠረጴዛ ስር ቀብረውት የተመለሱና በነሱ ላይ የነበረውን የህዝበ ክርስቲያኑ የተስፋ ጫላንጭል ያደፈኑበት ሆኖ ነው ያየሁት፡፡

በጠቅላይ ምንስቴሩ ሰብሳቢነት የተካሄዱት ሁሉ አገር አቀፍ ስብሰባወች በመላ ኢትዮጵያ የፈሰሰውን የኢትዮጵያውያንን ደም የተቃጠሉትን አብያተ ክጽቲያን ባለማንሳታቸው፤ የምናየው ምስል የምንሰማው መርዶ ቅዠት ነው ካልተባለ በቀር፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን በመቅበራቸው የተስማሙ ይመስላሉ፡፡

በፕሮቴስታንቱ ስብሰባ ላይ ጥቅላይ ምንስቴሩ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በመገንባት መንግሥትን አለመጠየቋን በጥሩ ምሳሌነት ኦርትሆዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ከመጥቀሳቸው በቀር፡ ስለተቃጠሉት ስለታረዱት ስለተፈናቀሉት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች  የተናገረ ወይም ያነሳ አንድ ሰው አልነበርም፡፡

እንዲያውም ጭራሽ ይህ ሁሉ እልቂትና ቃጠሎ በሚካሄድባት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉም አይመስሉም፡፡ ሁሉም በጠቅላዩ ስለተደረገላቸው ውለታ በማመስገን ቀረን የሚሉትን የቅንጦት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ላይ ለደረሰባት ሁሉ ግፍና በደል የሕሊና ጸሎት ሲጠበቅባቸው ያቀረቡት የይሟላልን ጥያቄ እንኳን ደረሰብሽ የሚል ሽርደዳ የሚመስል ነበር፡፡

እንዲያውም ጠቅላይ ምንስቴሩ በየስብሰባወች ባደረጓቸው ንግግሮች ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ በማድረግ ግድያውን ቃጠሎውን ጥፋቱን ሁሉ ሰብበው በዘመናችን ባሉት ፓትርያርክና ጠቅላይ ስራአስኪያጁ በማሸከም በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እጽፍ ድርብ በደልና ግፍ የፈጸሙባት መሰለኝ፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ጥለዋት ወደ ሌላ ቤተ እምነቶች የሸሺ ሁሉ፡ የሸሹት እውነት ክርስቶስን ፍለጋ ከሆነ ይህን ሸርና ደባ ሲመለከቱ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናቸው የሚመለሱ ይመስለኛል፡፡

የተደረጉት ሁሉ ስብሰባወች ቤተ ክርስቲያናችንን በጠርጴዛቸው ስር ቀብረዋት በተመለሱት ጳጳሳት ላይ የከረረ ጥላቻ እንድንፈጠርና በመካከላችንም ጳጳሳቱን በመደገፍና በቃወም ጎራ ተሰልፈን በመከፋፈል በእርስ በርስ ጭቅጭቅ እንድንጠመድ ለማድረግ የተሰራ ደባ መሆኑን መረዳት ያለበን ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል በሁሉም ስብሰባወች ጠቅላይ ምኒስቴሩ ራሳቸውን ፊደል አስቆጣሪ መምህር ለዓድዋው ድል መራሂት የነበረችውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በመምራት ላይ ያሉትን ጳጳሳት ፊደል ቆጣሪወች በማስመሰል ቤተ ክርስቲያናችን ኢትይጵያን ስታንጽና ስትገነባባቸው የነበሩትን ስርአቶች የጨው ካብ አደረጓቸው፡፡

“የጨው ካብ ሲናድ ሞኝ ይልሳል ብልህ ያለቅሳል” የሚለው አብባል ትዝ አለኝ፡፡ ዛሬ የጨው ካብ ላደረጓት ቤተክርስቲያናችን ለኢትዮጵያ መሠራትና መገንባት ባለቤት በመሆኗ አገር ናት እያሉ ተናግረውላት ነበር፡ የሚንዷትንና የሚልሷትን እየታዘብኩ ከሚያለቅሱት ጋር በመሰለፌ ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊነቴ ማረጋገጫ ስለሆነኝ የሕሊና እርካታ አግኝቸበታለሁ፡፡

በዚህ ሁሉ ዳሰሳ ላይ ስለሁ፡ እንዳግጣሚ የዘመናችን ምሑራን ስለ ሀገር በሚነጋገሩበት አውድ ላይ አቶ ጸሐይ ደመቀ “Quantum physics and the Quest for the Elusive National Dialogue in Ethiopia” በሚል ያዘጋጁትን ተመለከትኩ፡፡ ይህ ደግሞ አጼ ምንይልክ ለድሉ የተጠቀሙበትን ማርያማዊ አዋጅ እንዳቀርበው የበለጠ ገፋፋኝ፡፡

የአጼ ምንይልክ ማርያማዊ መርሆ

ፊታውራሪ ወልደ ሐዋርያት ስለ አድዋው ድል የውጤቱን ድምር በሕይወት ታሪካቸው በገለጹበት 75ኛው ገጽ ላይ “የሴቶችን አገልግሎት ስገምት የበቅሎወች አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨreሻ የአድዋ ድል ድምር ስገምተው የተገኘው በሴቶች አገልግሎትና በበቅሎወች ብርታት መሆኑን ይታወቀኛል”(57)፡፡ አሉ፡፡

አገርና ዐለም አቀፍ የሰፊና ጥልቅ ባህርይ ጥንቅር ያለው የአድዋን ድል የመሰለ ትንግርት ቀርቶ፦ ባንድ ዘመን ባንድ ትውልድ ባንዲት ወረዳ የምትፈጸም ክስተት በብዙ ዘርፎች ትገለጻለች፡፡ የአድዋው ድል የምትገለጽባቸውን ብዙ ዘርፎችን ለሚመለከታቸው ሊቃውንት ትቼ በወቅቱ የነበሩት መንፈሳውያን አባቶቻችን በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት ላይ በቀረጹት በማርያማዊው መርኋቸው ላይ ብቻ ላተኩር እወዳለሁ፡፡

አጼ ምንይልክ የተከተሉት ማርያማዊ መርሆ ታሪካዊ መሠረቱ ምን ነበር?

አጼ ምንይልክ ማርያማዊ መርኋቸውን ከየት አመጡት? እንዴትስ ከብሔራዊው አረበኛነትና ነጻነት ጋራ በማገናኘት ለሕዝብ መቀስቀሻ ተጠቀሙበት? በሰፊው ህዝብ አዕምሮ ላይ የቀረጹት በዚያ ዘመኑ የነበሩት የካህናቱን ሚና ምን ይመስል ነበር? በዚያ ዘመን የነበሩት ካህናት ይህን ማርያማዊ የድል መርሆ ከየት አመጡት?

እነዚህ ሁሉ ጥያቄወች ማርያማዊ መርሆ ከዚያም በፊትም ሲካሄድ ኖሮ በቅብብሎሽ የመጣ እንጅ በአጼ ምንይልክ ዘመን ብቻ ድንገት የተከሰተ አልነበረም፡፡ በአጼ ምንይልክ ዙሪያ ለነበሩት የጦር መሪወችና ለሕዝቡ አዲስ ባለመሆኑ የነበረው ህዝብ በካህናቱ የተሰበከውን ማርያማዊውን መፈክር አጼ ምንይልክ በአዋጅ መልክ ሲያቀርቡት ወዲያውኑ በመቀበል ወደ ተግባር ለውጦታል፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩት ካህናት በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት የቀረጹትን ማርያማዊ መርሆ “በክንዱ ኃይል አድርጓል ተቢተኞችን በተናቸው ግዠወችን ከዙፋናቸው አወረዳቸው የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው ባለጠጎችንም ባዷቸውን ሰደዳቸው፡፡ ለአባቶቻችን ለአእብርሃምና ለዘሩ እንደተናገረ ”(ሉቃ 1፡51_54) ብላ ቅድስት ድንግል ክርስቶስን ስትጸንሰው ከትናገረችው የተወሰደ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ማርያማዊ መግለጫ እንዳይዘነጋ በጸሎት ሰይማ በየቀኑ በመድገም መመሪያችን እንድናደርገው በጭንቅላታችን እንድንቀርጸው በቃላችን ደጋግመን እንድንናገረው አድርጋናለች፡፡

ኃይል የሚጠይቅ አዲስ ነገር ለማድረግ ከመሰማራታችን በፊት በጥበብ በልምድ በትምህርትና ከኛ ወደ ላቁ አባቶች ሄደን በፊታቸው ተንበርክከን የምንሸኘው በጸሎተ ማርያም (በመቤታችን መግለጫ) ነው፡፡ በነአጼ ምንይልክ የተፈጸመውን ይህን ማርያማዊ መፈክርም ሆነ ሌሎችን ሁሉ ቅርሶች ጥንታውያን መሆናቸውንና ከነሱ በፊትም የነበሩ መሆናቸውን የምናውቀው እስካሁን ድረስ በመካሄዳቸው ነው፡፡

እመቤታችን ክርስቶስን ስትጸንሰው የተናገረችውን ከየት ወሰደችው? መሠረታዊ ታሪኩስ እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ መነሳት አይቀርም፡፡ መቼ፡ ማን እንደጀመረውና እንዴት ወደኛ እንደተሻገረ መገለጽ ቢኖርበትም፤ ሰፊ ሐተታውን በዚህች አጭር ጦማር ማቅረብ ስለማይቻል፤ ከዚህች ጦማር በኋል ለማስከተል አዘግይቼ፤ ወቅቱን ወደ ሚያሳየው፡ ኢትዮጵያውነትን ሁለንተና ወደሚጠቁመው፡ በመናድ ላይ ያለውን ስርአት ወደ ተሸከመው ወደ ቅኔው ትምህርት እሻገራለሁ፡፡


የቅኔው ትምህርት

የቅኔውን ትምህርት የጠቀስኩ አዳዲስ ሐሳብ በማመንጨት ስለሚረዳ ነው፡፡ የቅኔው ትምህርት እንደ ዜማው ትምህርት በምልክት የተቀየደ አይደለም፡፡ በተፈጥሮና ባካባቢው የሚከሰቱትን አዳዲስ ክስተቶችን ለማሳየት የሚረዳው የቅኔው ሥርአተ ትምህርት በመሆኑ እንጅ ዜማውም ለኢትዮጵያ ውበት ከሰጡት ኪነታት አንዱ መሆኑን በመዘንጋት አይደለም፡፡

መንፈሳዊያን አባቶቻችን በአጼ ምን ይልክ ጭንቅላት ላይ የቀረጹት “ማርያማዊ መርሆ” ቅድስት ድንግል ማርያም ክርስቶስን ስትጸንሰው ካሰማቸው መግለጫ ወስደው ነው፡፡ መርሆውን በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት ላይ መቅረጽ ብቻ አይደለም፡፡ በዘመኑ የነበረው መገናኛ ያብነቱ ተማሪወች ነበሩ፡፡ ባላአገር አዳዲስ ሀሳብ የሚያገኘው ርስበርሱ የሚናበበው የጉባኤውን ትምህርት ለመማር አበባ እንደሚቀስሙ ንቦች ከደብር ወደ ሌላ ደብር ከአገር ወደ ሌላ አገር በሚዘዋወሩት የቅኔ ተማሪወች አማካይነት ነበር፡፡ በጠላትም አስቀድመው የሚገደሉት እነሱ ነበሩ፦

“ካህን ሞተ ተብሎ አይነግሩም አዋጂ
እንዲያው በየደብሩ መላክ ነበር እንጂ” ተብሎላቸዋል፡፡

ከቅድስት ድንግል ማርያም መፈከር (መግለጫ) የተወሰደው ማርያማዊው መርሆ ከአርባኛነተቻን (40ኛ) ጋራ የተያያዘ በመሆኑ ቦበታው ለመገለጽ አሁን አልፈዋለሁ፡፡

በዚህች ጦማር ከኢትዮጵያዊው አርባኛነት ጋራ ተዛምዶ በቅኔያችን ሲነገር የሰማሁትን ከዚህ ቀደም ባቀርበውም ከቅኔው ትምህርት ጋራ ንክኪ ያላቸው ኮፌዳውንና ከየመንደሩ እየዞርን የምንሰበስበው ምግቡ ሁሉ የተያያዘ ነውና አሁንም አቀረበዋለሁ፡፡

ኮፌዳዋ

ወደ ቅኔው ትምህርት በጥለቀት ከመግባቴ በፊት ላስኳላው ተማሪወች መምህሮች ላስታውሳችሁ የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ ይኸውም ስለ ሕዝባዊ ግንባታ በምትነጋገሩበት አውድ ላይ “Quantum physics and the Quest for the Elusive National Dialogue in Ethiopia” በሚል በአቶ ጸሐይ ደመቀ የቀረበው ነው፡፡

በአቶ ጸሐይ ደመቀ የቀረበውን የQuantum physicsን ትንታኔ በአዕምሯችሁ ቋጥራችሁ አባቶቻችን የኢትዮጵያዊነትን ሁለንተና የሰሩባቸውንንና የገነቡበባቸውን ከዚህ በታች የማቀርባቸውን ስልቶች ብትመለከቱ ራሳችሁን የምትታዘቡ ይመስለኛል፡፡

ከኮፌዳዋ እጀምራለሁ፡፡ ከየቤቱ የምንሰበስበውን ምግብ የምንይዝባት ኮፌዳችን ከቄጠማ ወይም ከሰሌን እንሠራታለን፡፡ ኮፌዳችንና ከየቤቱ የምንለምነው ምግብ ለሰምና ወርቅ ቅኔ ትምህርታችን የሚሰጡን ቅድመ ዝግጅት (orientation training) ነው፡፡

ኮፌዳችን ለኢትዮጵያ መግለጫ ሰም በመሆን ታገለግላለች፡፡ ኢትዮጵያ ለኮፌዳዋ ወርቅ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያን ወርቅ ኮፌዳዋን ሰም በማድረግ የቅኔውን ትምህርት እንጀምራለን፡፡ ኢትዮጵያን የምትወክለው ኮፌዳችን በሰበነክ አይጦች ከተደፈረች ኢትይዮጵያውያን ይበተናሉ፡፡ ይላሉ፡፡ ቅኒያችን ወራራወችን በሰበነክ አይጦች ይገልጻቸዋል፡፡

ባዶ ኮፌዳ ተሸክመን ከጎጇችን ስንወጣ ባዶነት አይሰማንም፡፡ በየደጃፉ ቆመን  እንተስማ ለማርያም ስለ እማምላክ ብለው” እያልን የምናሰመውን የእመቤታችንን ስም ስንቅ በማደረግ ነው፡፡ “ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ” የሚለው የአድዋው ጦርነት የታጀበት የናቶች እንጉርጉሮ የተወሰደው ካብነቱ ተማሪወች ነው፡፡

ከየቤቱ በስሟ የምንሰበስበው ምግብ ወደ ኮፌዳችን ሲገባ ስሙ ይቀየራል፡፡ ውጥንቅጥ ይሆናል፡፡ ኮፌዳችንን ኢትዮጵያን የምትወክል ሰም እናደርጋታለን፡፡ በኮፌዳችን ሰብስበን የያዝነውን ውጥንቅጥ ህዝቡን የሚወክል ወርቅ እናደርገዋለን፡፡ ኢትዮጵያን በሰምነት የምታገለግለን ኮፌዳችን እንዳትቀደድ አይጥ በማትደርስበት ቦታ እናስቀምጣታለን፡፡ ኮፌዳችን በሰምነት የምትገልጻት ወርቂቱ ኢትዮጵያ ዳርድንበሯ እንዳይቀደድ እንድንጠነቀቅ መምህሮቻችን ያስጥነቅቁናል፡፡

ከላይ እንዳልኩት ከተለያዩ ቤቶች ሰብስበን በውስጧ የከተተነው ምግብ አንድ አይነት አይደለም፡፡ ወደ ኮፌዳችን ሲገባ ስሙ ተቀይሮ ውጥንቅጥ እንለዋለን፡፡ ውጥንቅጥ የሚለውን ቃሉን ለሁለት በመሰንጠቅ ሰምና ወርቅ በማድረግ እንቀኝበታለን፡፡ “ውጥን” ማለት ጅምር ሲሆን “ቅጥ” ማለት ደግሞ ቅርጽ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ሲደመሩ “embryo”ማለትም የጅምር ቅርጽ ማለት ነው፡፡ “ወጥቅጥ” ማለትም ይሆናል፡፡ 

በየቤቱ እየዞርን የምናሰማው የልመና ድምጽ “በእንተ ስማ ለማርያም፡ ስለ እመአምላክ ብለው” የሚለው ነው፡፡ በዚህ የልመና ጥሪ ድምጽ ከተለያየ ቤት የምነሰበስበውን የተለያየ ምግብ “ውጥንቅጥ” የሚለው የምግቡ ስም ከነጠላው ሰምና ወርቅ ቅኔ ትምህርታችን ሌላ ሠረዝ ለሚባለው ቅኔ መሠረትነት አለው ነው፡፡ “ ውጥንቅጥ” ማለትም “ድብልቅልቅ” (ቅልቅል) የሚል ትርጉም አለው፡ ከነጠላ ሰምና ወርቅ በላይ እንደቀይ ሽንኩርት የተደራረቡና የተነባበሩ ብዙ ወርቆችና ብዙ ሰሞች ማለት ነው፡፡ ይህም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመላ ኢትዮጵያውያንን ሰውነት የተሸክመ መሆኑን ያሳያል፡፡

ውጥንቅጥ የሚለው ከሁለት ቃላት የተጣመረ ይሆንና ሌላም ትርጉም አለው፡፡ “ውጥን” ማለት ጅምር ሲሆን “ቅጥ” ማለት ቅርጽ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ሲደመሩ በቀጥታ የተጀመረ ማለት ሲሆን የቅኔያችን ቅርጽ ኢትዮጵያዊነት በቀጥታ የተጀመረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥየ ቅኔውን ውስጣዊ ይዘት እዳስሣለሁ፡፡

የቅኔው ይዘት

የቅኔ መጀመሪያ መቁጠሪያችን ፊደል ጉባዔቃና ትባላለች፡፡ የሕብረተ ሰብ ጅምር የሆነችውን አንዲትን ትዳር እንገልጽባታለን፡፡ በሰውነታችን አንዲት nucles የምትባለው ሕዋስ “structures that contain the hereditary information” እንደ ምትባለው ጉባዔቃናም የህብረተ ሰቡ ስሪት ለሚገለጽበት ማሕበራዊ ቅኔ መነሻ ናት፡፡ 

ጉባዔቃና አራት ሐረጎች ሁለት ቤት መምቻ ግጥሞች አሏት፡፡ አንዲት ማሰሪያ ግሥ (verve) አላት፡፡ በባልና በሚስትነት የተዋቀረችውን አንዲት ትዳር ትወክላለች፡፡

ባል ካንድ ቤት መጥቶ፤ ሚስት ከሌላ ቤት መጥታ በመጣመር የሚመሠረቱትን ትዳር ያሳያል፡፡ ባልም ሚስትም ከወንዱና ከሴት አያቶቻቸው የተገኙ ናቸው ፡፡ ይህም ማለት አራት ትውልዳውያን ሐረጎች መጥተው በመጋባት ባንዲት ጎጆ ከሚኖሩ ባልና ሚስት የተወለደው አንድ ኢትዮጵያዊ ለአካላዊ መራራቅ መሰብሰቢያና ማሰሪያ ግስ ነው ማለት ነው፡

በግእዝ ቋንቋ የምንማረው የቅኔው ስልት ከአማረኛው ስነ ጽሑፍ ይልቅ እጅግ የጠለቀ ነው፡፡ የአማረኛው ስነ ጽሑፋችንም ቢሆን ሆን ተብሎ ስለተዘመተበት ዛሬ ይዳከም እንጅ ከግእዙ traditional grammar ጋራ እየተወዳደረ በመገስገስ ላይ ነበር፡፡

በአማርኛ ሰዋሰዋችን በተመሳሳይ ፊደላት የሚገጠሙትን ብንሰርዛቸው ስድ ንባብ ይሆናል፡፡ በግጥም የተዘጋጀውን ሀሳብ ቤት መታ ሲባል ያልገጠመውን ስድ እንለዋለን፡፡ ቤት በመታ ግጥም በሕገ ተፈጥሮ በትዳር መስመር የተሰለፈውን ዜጋ እንገልጸዋለን፡፡ በግጥም ቤት ባልመታ ስድ በሚባለው ሀሳብ ትዳር ያልያዘውን ዜጋ እንገልጸዋለን፡፡

በጉባኤ ቃናዋ ያሉት አራቱ ሐረጎች ባባትና በእናት በኩል ያሉትን የወንድና የሴት አራቱን አያቶች የወክላሉ፡፡ ያንድ ኢትዮጵያዊ አያቶች ካንድ ነገድ ወይም ጎሳ ብቻ የተቀዱ ሳይሆኑ በግድም ሆነ በውድ በማወቅም ሆነ ባለመወቅ ከየቤቱ እንደምንሰበስበው ምግብ እየተቀላቀልንና እየተወናቀጥን የመጣን መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

በዚህ ስሌት የሚያድገው የመጨረሻው ቅኔያችን በስምንት ቤት ግጥም የተዋቀረው መወድስ የሚባለው ነው፡፡ በጉባኤ ቃናችን አራት የወንድና የሴት አያቶችን ዘር ስንከተል ወደ ስምንት ቤት የሚደርሰውን የዘር ስርጭት ይወክላል፡፡ ይህም ማለት ከስምንት ቤት በኋላ የትውልዳችንን የዘር ግንድ መሰብሰብ ወደ ማንችልበት ሐርግ መገባታችንን የሚጠቁም ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፡ በባህል፡ በሃይማኖት፡ በወንዝና በሸንተረር ተበታትነን ብንኖረም በደምና ባጥንት ግኙነት የተሳሰርን እንደ ቀይ ሽንኩርት የተነባበርን ሠረዞች መሆናችንን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ 

የተደራረቡ የሰምና የውርቅ ጥንቅሮች ዋና ማሰሪያቸው አንዲት ቃል ግስ ወይም verbe መሆኗን በጉባዔ ቃና እንዳየነው፡ መወድስ በምንለው ሰፊ ሠረዝ ቅኔ ሰፊውን አካላት በእኩል ደረጃ የምትገልጽው አንዲት ግስ ናት፡፡ ይህችን ግሥ “dichotomy” የምትለው ቃል ከሞላ ጎደል የሚገልጻት ይመስለኛል፡፡ እጽፍ ድርብ “dichotomy” የሆነችው ቃል እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የምትወክልና የምትገልጽ ናት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ dichotomized (ሕብር) ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ራሱን dichotomized እያደረገ ኢትዮጵያዊውን ሕብረተ ሰብ ሲገነባ ኖሯል ይላሉ፡፡

እንደ ቀይ ሽንኩርት የተደራረበ ሕብረተ ሰብ (ሕብረተ ሰባዊ ግንባታ)

በግእዝ ቋንቋ የምንማረው ቅኔ የሕብረተ ሰቡን ስሪት በጥልቀት እንደሚገልጸው አይተናል፡፡ የአማረኛው ስነ ጽሑፋችን የሕብረ ሰባዊነታችንን ሠረዛዊ ድርብርብነት በአቶ ጸሐይ ደመቀ ከቀረበው ከQuantum physics ትንታኔ ባላነሰ ፈሊጥ ይገልጸዋል፡፡

Quantum physics ትንታኔ በአዕምሯችሁ ቋጥራችሁ አባቶቻችን የኢትዮጵያዊነትን ሁለንተና የሰሩባቸውንና የገነቡበባቸውን ከዚህ በታች የማቀርባቸውን ስልቶች ብትመለከቱ ራሳችሁን የምትታዘቡ ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በታች በስድስት ዝርዋን ቃላት በሚጠናቀሩ አገባቦች ሕብረሰባዊነታችንን አማረኛ ሰዋሰዋችን እንዲት እንደሚገልጸው እንመልከት፡፡

1ኛ ባለ፡ 2ኛ፦ጋራ፡ 3ኛ፦አምጣ፡ 4ኛ፦ደም፡ 5ኛ፦አገር፡ 6ኛ፦ቤት ናቸው ፡፡ በጥንቃቄ ትኩረት ተራ በተራ እንያቸው፡፡

1ኛ ባለ፦ባለ የምንላት ሁለት ፊደላት ከቀሩት 5ቱ ቃላት ጋር እየተደመረች የሕብረተሰቡን ጥንቅር ትገልጻለች፡፡
2ኛ ባለ_ጋራ፦ የምትለው ሁለት ፊደል ከጋራ ጋራ ስትደመር፡ አንድ ቃል ባለጋራ ትሆናለች ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከሰውነቱ ከደሙ ካጥንቱ ጀምሮ ከሰውነቱ ውጭ በኢትዮጵያ ምድር እስካለው ቆስቁስ ድረስ የማይጋራው የግሉ የሆነ ነገር የለውም፡፡ ማለት ነው፡፡
3ኛ ባለ_አምጣ (አንጣ) ማለትም ፦ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የማይወራረሰው የማይወሳሰደውና ማይቀባበለው አምጣልኝ ላምጣልህ የማይባባለው የለም፡፡
4ኛ ባለ_ደም፦ኢትዮጵያው ከሌላ ጋራ የማይጋራው ንጹህ ወጥ የሆነ ደም የለውም፡፡ ሁሉም ለሁሉ የደም ባለቤት ነው፡፡
5ኛ ባለ_አገር፦እየንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ለተዘረጋቸው ኢትዮጵያ ባለ አገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገሩ ናት፡፡ በተለይም የዘመኑ ትምህርት ሲገባ ከተማነት እያየለ ሲሄድ ባላገርነት ያለመሰልጠን የኋላ ቀርነት መገለጫ መሰደቢያ እየሆነ መጣ፡፡
6ኛ ባለ_ቤት፦ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጠረፍ እስከጠረፍ በተዘረጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በደረሰበት ባለቤት ነው፡፡ የአማረኛችን ስነ ጽሑፍ እንደሚያመለክትን ሁለት ባህርያት ስድና ግጥም የምንላቸው አሉን፡፡ ስድ ማለት በትዳር ግጥምጥም ያልተወሰነውን ሰው ሲያሳይ ግጥሙ ደግሞ ከተለያዩ ቤቶች የተወለዱ ዜጎች ተጋጥመው የሚኖሩትን ጋብቻ ያመለክታል፡፡ ቤታ መታ ይባላል፡፡

ጠላቶች በየዘመናት ኢትዮጵያን ሲያፈርሱና ሕዝቡን ሲበታትኑት በየዘመናት የነበሩ ሊቃውንት ኢትዮጵያውያን ደግሞ መልሰው ህዝቡን የሚያስተሳሩባቸውና ኢትዮጵያን የሚገነቡባቸው እስካሁን የተገለጹትን ሕዝቡ ወደ ተግባር የሚለውጡባቸው እሴቶች የሰንበቴና የጽዋዕ ማኅበራትም ነበሩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ እነዚህንም እሴቶች ልንዳሣቸው ይገባል፡፡

በቅኔው በሰዋሰው የተሠራው ሕዝባዊ ስሪት የተገነባበት ሌላው ዘዴ ሰንበቴና የጽዋዕ ማህበራት

 ሕብረተ ሰቡ በየወሩ የሚገናኙባቸው የጽዋዕ ማሕበራት በየሳምንቱ የሚገናኙባቸው ሰንበቴወች አሉ፡፡ በማርያም በጻድቃን በሰማእታትና በመላእክት ስም በ12 ቁጥር ተወስነው በየሳምንቱ የሚገናኙባቸው የጽዋ ማህበራት አሉ፡፡ ማሕበራቱ በቀኑ ሰአት በአመቱ ወራት በሐዋርያትና በ12 ነገደ እስራኤል ቁጥር ልክ በሙሴ ስም የተዋቀሩ ናቸው፡፡

የቀኑን ሰአት የአመቱን ወራት የሐዋርያትንና የነገደ እስራኤልን ቁጥር ለመግለጽ ብቻ አይደለም፡፡ ሶስቱ ስላሴንና አርባእቱ እንስሣን እያስታወሰን እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ እያልን ከምንጸልይባቸው በአራቱ ጣቶቻችን ላይ ካሉት 12 አጽቆቻችን ጋራ የተሳሰሩ ናቸው፡፡

በአራቱ ጣቶቻችን ላይ ያሉት 12 አጽቆች ባንዲት ጣታችን ላይ ላሉት ለ3 አጽቆች ሲካፈሉ አራት አጽቆች ይደርሳሉ፡፡ ጸወርተ  መንበሩን አራቱን እንስሦች ያመለከታሉ፡፡ እንደገና በአራቱ ጣቶቻችን ላይ ያሉትን 12 አጽቆች ለአራት ጣቶቻችን ሲካፈሉ በመንበረ ጸባዖት ላይ ያሉትን ስላሴወችን ያመለክታሉ፡፡

በእንተ ማርያም መሐረን ክርስቶስ” ብለን ጸሎታችን የምንዘጋው በሙሴ ሊቀመንበርነት በሚመራው በጽዋ ማህበራት አባላት ቁጥር፡ በሰአተ መአልቱና በሰአተሌሊቱ ቀመር ባመቱ 12 ወራቶች፡ በሐዋርያትና በ12 ነገደ እስራኤል ቁጥር ልክ ነው፡፡ ለምን ከሙሴ ጋራ ተያያዘ ለሚለው ከላይ እንዳልኩት ሐተታው ሰፊ ስልሆነ በሚቀጥለው ጦማር ለመግለጽ በማለፍ እስካሁን የተገለጹት ስርአታት መቼና እንዴት እንደፈረሱ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

መቼና እንዴት ፈረሱ?

መቼ ፈረሱ፦ያስኳላውን ትምህርት ይዘውት የገቡ ፈረንጆች ትምህርቱን በመጀመሪያ በተማሪወቻቸው ጭንቅላት ማስረጽ በጀመሩበት ወቅት መፍረሱ ተጀመረ፡፡ በዶክተር ክነፈርግብ ዘለቀ ሰብሳቢነት በተዋቀረው በጊዜአዊ ተሐድሶ ጉባኤ መሳሪያነት የካቲት 10 ቀን 1968 የደርግ መንግሥት በገሀድ አፈረሳቸው፡፡

ዶክተር አረጋዊ በርሔ “A Political History of the Tigray people’s Liberation Front (1975-1991)” በሚል ርእስ ለDoctoral dissertation (page 300) ወይም ባሳተሙት መጽሀፋቸው (page 246) ላይ እንደተገለጸው የማፍረሱ ተግባር ተፈጸመ ፡፡

“Thirdly, the TPLF launched a series of conferences or ‘seminars’ for selected parish priests in 1979 to win them over The underling motive of the seminars was to isolate the church in Tigrai from the wider Ethiopian church in order to foster Tigrian nationalism along the line of the TPLF’s strategic objective. Suppressed Tigrian nationalism was invoked to challenge the dominant Ethiopian Orthodox Church. The initial woreda seminars for priests were conducted by an eloquent TPLF fighter, Gebre Kidan Desta., a graduate of The Theological College at Addis Ababa University። The themes of the seminar were to replace the Ethiopian Church’s authority by a TPLF- minded church and the language in the church with Tigrigna and, ultimately to further Tigrian nationalism and identity. This process involved the mobilization of parish priests and ordinary Christians to isolate them from the church’s national hierarchy. To weaken church authority, an intelligence group was formed under Sibhat Nega to infiltrate the well-established monasteries in Tigrai such as Debre Damo, by planting TPLF members camouflaged as monks and influencing church activities in the interests of the TPLF. . In 1987 and 1989, regional and national conferences for priests were organized by the TPLF in the liberated territories to reshape the Tigrai church in line with the TPLF programme.” A separate secretariat of the Orthodox Church was formed in the liberated areas of Tigrai and was supposed to operate under the TPLF guidelines. Practically, the Ethiopian Church was divided in to two separate secretariats, one under the regime and the other under TPLF. Both worked in Tigrai until 1990, when the TPLF overran Meqele, the capital of Tigrai. The regime’s secretariat fled Meqele for Dessie and the secretariat in the liberated territories entered Meqele and operated until the TPLF seized power in1991.”

ወደ አማሪኛ ሲተረጎም

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። 

ቤተክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።

የወረዳ ስልጠና የተጀመረው በጠንካራ ትግሉ የታወቀው ካዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነገረ መለኮት ትምህርት የተመረቀው ገብረ ኪዳን ደስታ ነው። የስልጠናውም ይዘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላላ መዋቅራዊ አስተዳደር በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለሟሎች መተካትና በቤተ ክርስቲያኒቱ አካባቢ የትግርኛ ቋንቋ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።

በዚህ መንፈስ ተቀረጾ የተዘረጋው እቅድ በየሰበካውና አጥቢያው ያሉትን ቄሶችና ምእመናኑን ቤተ ክርስቲያኒቱ ጠብቃ ካቆየችው ታሪክና ብሄራዊ መዋቅር እየገነጠሉ በመስኮብለል ወደ ነጻ አውጭው አምባ መሰብሰብ ነው። መነኮሳት በመምሰል ደብረ ዳሞ ወደ መሳሰሉት ገዳማት ሰርጎ በመግባት የድርጅቱን እቅድ በማስተጋባት የሚያዳክም አጥኝ ኃይል በስብሀት ነጋ መሪነት ተመሰረተ። የማሰልጠኑ ተግባር ከተፈጸመ በኋላ፤ የሰለጠኑት አስመሳይ መነኮሳት በትግራይ ምድር ዙሪያ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ከዋናው ጽፈት ቤት መገንጠልን በ1987 እና በ1989 ተግባራዊ እንዲያደርጉት አደረገ።

ከነጻ አውጭው አመራር የሚቀበለው መነኮሳት እየመሰለ ሰርጎ የገባውአስመሳይ ቡድን፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መዋቅር ተገንጥሎ ከነጻ አውጭው ጋራ ጎን ለጎን የማካሄ ስራውን ቢሮ ከፍቶ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ከዋናው ጽ ቤትና ከነጻ አውጭው ትእዛዝ በሚቀበሉት ቡድኖች መካከል የጎላ ልዩነት በግልጽ መታየት ጀመረ። እስከ 1990 ድረስ ሁለቱም ጎን ለጎን ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ፤ ነጻ አውጭው መቀሌን ሲቆጣጠር፡ ከዋናው ጽ ቤት አመራር ይቀበል የነበረው መቀሌን ለቆ በ1991 ወደ ደሴ ሲሄድ፡ በነጻ አውጭው ስር ይመራ የነበረው ቡድን መቀሌውን እንዳለ ተረክቦ ተቆጣጠረ”፡፡

አጼ ምንይልክ በአድዋ ድል የተቀዳጁበትን ማርያማዊ መርኋቸውን መነሻ በማድረግ በተከታታይ ሳምንታት በጠቅላዩ መሪነት የተደረጉትን ስብሰባወች በዚህች ጦማር ዳሰስኳቸው ተመለከትኳቸው፡፡ 

ማርያማዊ መርሆውን በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት ያሰረጹት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ኢትዮጵያን ያነጹባቸውንና የገነቡባቸውን ስርአቶች ፈተሽኩ፡፡ በዚህ ዘመን ላይ ያለነውን ካህናት በተለይም ሲኖዶስ በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት ላይ ማርያማዊ መርሆውን ከቀረጹት ሊቃውንት መንፈሳውያን አባቶች ጋራ አነጻጸርኩ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዚህ ዘመን ያለነውን ካህናት ባዶነት ተገነዘብኩ፡፡

የዘመናችን ምሑራን ስለ ሀገር በሚነጋገሩበት አውድ ላይ “Quantum physics and the Quest for the Elusive National Dialogue in Ethiopia” በሚል ርእስ በአቶ ጸሐይ ደመቀ ቀርቦ፡ ባጋጣሚ ያየሁትን የዘመናችን ፍልስፍና ጥንታውያን አባቶቻችን ኢትዮጵያን ካነጹባቸውና ከገነቡባቸው ስልቶች ጋራ አወዳደርኳቸው፡፡ በዚህ ዘመን ተማርን የምንል ሁሉ ያስኳላ ተማሪወች ከጥንታውያን ሊቃውንት አባቶቻችን ልንሻል ቀርቶ ከደረሱበት መድረስ ያልቻልን ኋላ ቀሮች መሆናችንን ተረዳሁ፡፡

በጠቅላዩ በተቃኙ ከአድዋው የመተሳቢያ በዐል ጀምሮ እስከ ሙስሊም ወገኖቻችን ተከታታይ ስብሰባወች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተዘመተባት ከዚህ በላይ በተገለጹት ስርአቶች የኢትዮጵያን ሕብረተ ሰብ ስትገነባና ኢትዮጵያን ከወራሪወች ስትጠብቅ በኖረችው ኦርቶድክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ አይደለምን? ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በአጼ ምንይልክ ጭንቅላት ከቀርጹት አጼ ምንይልክ ድል ከተቀዳጁበት ከማርያማዊ መርሆ ሌላ ምን የፈረሰ ነገር አለ?

ለመቀጠል እዚህ ላይ ይቆየን፡፡

Tuesday 11 July 2023

“ኩሽ!” እያላችሁ ምን ያንኮሻኩሻችኋል?

“ኩሽ! እያላችሁ ምን ያንኮሻኩሻችኋል?

ወንድሙ መኰንን
England: 11 July 2023

ሰው ሲበድላችሁ፣ እስቲ አትናደዱ፤
ጠላትን አትጥሉ፣ ክፉን ሰው ውደዱ።
የክፉ ሰው ክፋት፣ ጠቃሚ ነው ትርፉ፤
ያነቃቃችኋል፣ እንዳታንቀላፉ።
የልቦናው ስሜት፣ እየተራቀቀ፣
ሁልጉዜ ወደ ላይ፣ በጣም እየላቀ፤
በሥራ በጥበብ፣ ግሎ ለመነሳት
ቆስቋሽ የፈልጋል፣ የሰው ልጅ እንደ እሳት
                                                                        ከበደ ሚካኤል፣ የዕውቅት ብልጭታ ገጽ 163

1)   1)   መግቢያ

ዳማ የተባለ ዳንግላ ፈረስ፣ ዋርዲት የተባለች ሽቅርቅር በቅሎ ጋር ሜዳ ውስጥ ሣር ሲግጡ ይተዋወቃሉ። መሽቶ ሊለያዩ ሲሉ፣ ዳማ በጣም ስለወደዳት ዋርዲትን “አባትሽ ማናቸው” ብሎ፣ ጠየቃት። ዋርዲት እየተሽኮረመመች፣ “አጎቴ ጥሪኝ የሚባል ፈረስ ነው” ብላ መለሰችለት ይባላል። ፊየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያ። ምን ለመደበቅ ነው?

ድንቁርና፣ ያጀግናል። ደፋር ያደርጋል። አንድ ሰው ባነበበ፣ በተመራመረ፣ ባወቀ ቁጥር ነው፣ አለማወቁን እየተረዳ ሲመጣ ነው ቁጥብ የሚሆነው። ያልበሰለው ጥራዝ ነጠቅማ፣ ጫፍ ይዞ እንደባዶ ቆርቆሮ ሲንጣጣ ነው የሚውለው። ከሠርቪስ ኮሊጅ ይሁን፣ ወይም ከነጻ ገቢያ ድግሪ እየገዙ፣ ያልበሰሉ የእፍ እፍ ባለ ዶክትሬት ዲግሪዎች፣ ታሪክቱን በጭንቅላቷ እያቆሙ ሲደፏት እያየን፣ አንዳንዴም በዝምታ፣ ካልሆነም በፈገግታ እያሳለፍናቸው ነው። በዝምታችን ምክንያት ምድሪቱ አልበቃ እያለቻቸው ነው። እንደልባቸው ይቀባጥራሉ። ፕሮፌሰሩ ዓይኑን በጨው አጥቦ፣ አንዳችም ሳያመነታ፣ “የመጀመሪያው ሰው ኦሮሞ ይባላል፣ ከውሀ ነበር የወጣው፣ ጾታ አልነበረውም፣ ዋቃ እንዲህ በጎን አይቶት ለሁለት ሰነተጠቀው” [i] እያለ ሲያወጋን ስቀን ወደሌላ መመልከት ግድ ሆነብን። ምንጩ ደሞ የኦሮሞ አፈ-ታሪክ ነው። የትም ተጽፎ የማይገኝ! ይኸው ፕሮፌሰር፣ ለብዙ ሺ ዓመታት በግዕዝ ተጽፎ የተቀመጠውን ታሪክ፣ የደብተራዎች ፈጠራ ነው እያለ ሲያጣጥል ሰምተነዋል። አባቶቻችን ፊደል ቀርጸው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ዳምጠው፣ ጽፈው ያስረከቡን ታሪክ፣ ተረት ሁኖ ከተገኘ፣ በነዚህ የዘረኞች ሊሂቃን ከተጣጣለ፣ የማይመስል አፈ-ታሪክ ዕውነትነት ሲኖረው ይታያችሁ! ወይ አለማፈር!

2)  2)  ሌሎች ምን ይላሉ፣ ስለኢትዮጵያ?

የኢትዮጵያን ታሪክ ብዙ የአውሮፓና የአሜሪካ ተመራማሪዎች ጽፈውታል። ከነዚህም ፐከንሀም (Thomas Francis Dermot Pakenham)፣ ኡላንዶርፍ (Edward Ullendorff) ፣ ክራሚ (Donald Crummey)ሳልቫዶሬ (Matteo Salvadore)፣ ፓንክረስት (Richard Keir Pethick Pankhurst)፣ ፓየዝ (Pedro Páez)፣ ማርኩስ (Harold Marcus) እና ብዙ ሌሎችም የጻፉትን የኛ ዘመናዮች ያጣጥሏቸዋል። “እኛን ኮሎኒ አድርገው ለመግዛት ስለሚፈልጉ፣ ኦሮሞን ዝቅ አድርገውና አንቋሸው ጽፈዋል” ይሉናል። እነ ፓየስ እኮ ያዩትን ነው የጻፉት። ፓይዝ የተባለው ፖርቱጋላዊ፣ የኢትዮጵያ ታርክ (História da Ethiópia) በተባለው በ1622 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፉ፣ የኦሮሞ ተዋጊዎችን ጭካኔ በዓይኑ ያየውን መዝግቧል። እና እንዲደብቁላቸው ነው የሚመኙት? ኢትዮጵያን በጣም የሚጠላው ባውም (James Edwin Baum) እንኳን፡ “አረመኔዋ ኢትዮጵያ (Savage Abyssinia) ብሎ በጻፈው ዘረኛ መጽሐፉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ኦሮሞውንም፣ አማራውንም ቢስድብም፣ ታሪኳን ግን እየመረረውንም ቢሆን እንዳለች እንዲህ ሲል ለማስቀመጥ ተገዷል።

Yemen, the Red Sea province of Arabia, was conquered by the Abyssinians who ruled that turbulent country until 570 A.D. About the year of Mohamet’s birth, they were defeated before Mecca and driven, bag and baggage for ever from the continent of Asia”[ii]

ወደ አማርኛ በቀላሉ ስናቀርበው፤ “አቢሲኒያ፣ የአረቢያ ጠቅላይ ግዛት የነበረችውን የተበጠበጠች፣ የመንን ወራ ከያዘች በኋላ፣ እስክ 570 ዓ.ም ድረስ አስተዳደረቻት። ሞሀመት በተወለደ ዘመን አካባቢ፣ ከመካ በፊት፣ ተሸነፈው፣ ጓዛቸውንና ጉዝጓዛቸው ሰብስበው ተባረሩ” ይለናል። የመን ድረስ ዘልቃ ያስተዳደረች ኃያል አገር መሆኗን መደበቅ አልቻለም።

የኛዎቹ የተማሩ መሀይማን ግን መኖሯንም ክደው ያልሆንቺውን “ኩሽ ነበርች” ይሉናል። ኩሽ እኮ ግብጾች ጥቁሮችን ለመስደብ የተጠቀሙበት ቃል ሆኑን እንኳን አያውቁም። መሀይምነት ጀግና ያደርጋል ያልኳችሁ ለዚህ ነው። ድፍረታቸው የሚገርም ነው። ሊያለያዩን፣ ሊበታትኑን፣ “ኩሽ! ኩሽ! ኩሽ ነን እኛ” ይሉናል። ማነው ኩሽ? “ከአቢሲኒያዎች የተለየን ህዝቦች ነን” እያሉ አንዳንድ በኢትዮጵያ ቆሽታቸው የደበነ ነጮች የጻፉትን አንጠልጥለው፣ ልባቸው ውልቅ እስኪል ድረስ ይንጣጣሉ። በዛ! እነሱስ እሺ ይንኮሻኮሹ፣ ሌሎቹን፣ እንደ ካፋ፣ ወላይታ ጋሞ፣ ሲዳማ፣ የመሳሰሉትን የደቡብ ብሔር ብሔርሰቦችን ምን በወጣቸው? ከጎናቸው ለማሰለፍ? ጅሎች እየመሰሏቸው ብዙ ርቀት ሂደዋል። እነዚህ ሰዎች፣ አንድ ቋሚ የታሪክ አሻራ ጥለው ያለፉት የሚታይ ነገር የላቸውም። የመጀመሪያውም ሀውልት ስለነሱ የተቀረጸው በኢትዮጵያ ጠላት የተጻፈ ልቦለድ ገጸ ባህርይ በአኖሌ ስም ነው። ቢሞቱ ይሻላቸዋል! ሲያሳፍሩ!

በዚያም አልተወሰኑም። ሱማሌውንም፣ አፋሩንም “ኩሽ ናችሁ” ብለው፣ የኢትዮጵያን ፊደላት ሳይሆን፣ ላቲንን፣ እንዲጠቀሙ አስታቅፈዋቸዋል። ወደሰሜኑም ብቅ በለው፣ ቅማንቱን፣ አገውን እና ሸናሻውን፣ ኩሾች ናችሁ እያሉ የአንዳንዱን ግልብ፣ ጭንቅላት አዙረዋል።

የአዋቂዎች ዝምታ፣ መሀይሞች እንደፈነጩበት ሰፊ ቦታ ሰጣቸው። ይፈነጩብናል። የታሪክ ተመራማሪ ኢትዮጵያውያን አፍረው ይሆን ወይም ድፍርት አንሷቸው አይታውቅም ዝምታን መርጠዋል። ንጉሡን ራቁታቸውን መሆናቸውን የሚነግራቸው እብድ ያስፈሊጋል። ግፋ ቢል፣ እብድ ቢባል ነው። ራቁታቸውን ናቸው ብሎ በመሸበት ማደር ይመረጣል! እኔ እሱን መሆን መርጫለሁ።

ከላይ ያለው የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ግጥም ያስቀመጥኩላችሁ፣ ዝም ብዬ አይደለም። ይነካኩን ይነካኩንና፣ አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ፣ ይበቃናል። እነሱ፣ ለተንኮል ያጣመመቱን ለመቃናት ግድ ይለናል። ለመሆኑ፣ ኩሽ ብለው እንዲህ የሚሟሟቱበት አቶ ኩሽ ሆዬ ማን ነበር? እስቲ በሚቀጥለው እንይ።

3)3)  ትክክለኛው የኩሽ ታሪክ

ነገር ከሥሩ፣ ውሀ ከጥሩ ይባል የለ?  እስቲ ወደ መሠሩቱ እንሂድ። መሠረቱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በከፊል፣ እስራኤላውያን የትውልድ አመጣጣቸውን ጥንታዊ ታሪክ ጽፈው አስቅምጠውልና። ሙሉ ግን አይደለም። የራሳችን ሊቃውንት እጀ የገቡ ብዙ በብራና ላይ የተጻፉ መጽሐፍት፣ መጽሐፈ ኼኖክ ሳይቀር እስከዘመናችን ዘልቀዋል። ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 ጀምሮ፣ ኖኅ 3 ልጆች እንደ ነበሩት ያወራል። እነሱም፣ ሴም፣ ካምና ያፌት ናቸው። ዣንሸዋ ተቀዳሚ የሚባለው ጥንታዊው መጽሐፈ ብሩክ የነዚህን ትውልዶች ከገጽ 261 እስከ 275 ዝንፍ ሳይል፣ የሴምንም፣ የካምንም፣ የያፌትንም ትውልድ ዘርዘሮ ያስቀምጥልናል። ሰረገላ ታቦር የተባለውም፣ በመሪ ራስ አማን በላይ የተተረጎመውም ከገጽ 290 ጀምሮ እስክ 306፣ ይኸንኑ ይተነትናል። ማንበብ የሚወድ፣ የታሪክም ተመራማሪ ሁኖ ከዩኒቨርሲቲ መመረቅ አያሻውም። ታሪኩን እንደወረደ አንብቦ ይረዳል። ማን የማን ልጅ እንደሆነ በተጻፈው መሠርት ማንበብ ነው። የሚያወሩት ስለካም ልጅ፣ ኩሽ ከሆነ፣ የሴም ልጆች ሴማውያን ከተባሉ፣ የያፊት ልጆች፣ ያፌታውያን ከተባሉ፣ የካም ልጆች ካማዊያን “አፍሪካ” ጋ ሲደርስ የማይባሉበት ምስጢር ከቶም አይገባኝም። አንድ መደበቅ ያለበት ታሪክ ከሌለ እንደ ዋርዲት ምን አጎት ድረስ ያወርዳል?

የኖኅ ልጆችን የትውልድ ሐረግ (Family Tree) ሲመዘዝ እንዴት ማመን ይቻላል? መልሱ ቀላል ነው።  ጥንታዊውያን ማንበብና መጽሐፍ የሚችሉ አባቶቻችን፣ ልጆች ሲወለዱላቸው፣ ቀኑና ዓመተ ዓለሙን/ምህረቱን ወይም በየአገሩ የዘመን አቆጣጠር ባህል መዝግቦ ማስቀመጥ ልማዳቸው ነው። ያልተማሩት ይኸ ዕድል የላቸውም። ለምሳሌ፣ ወላጅ አባቴ፣ አቶ መኰንን አየነው፣ ነፍሳቸውን ፈጣሪ በገነት ያኑርልኝና፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ውርስ ባህላቸው መሠረት፣  የኔን ልደት ከነ ሰዓቷ፣ ቀኗ፣ ወሯንና ዓመተ ምሕረቷን፣ ከደረታቸው በማትለየው ዳዊታቸው የውስጥ ሽፋኗ ላይ ጽፈው ቁጭ አድርጎልውኛል። ያ ብቻም አይደለም። የደብረ ኤሊያስ ካህናት ትውልድ በመሆናቸው ወደ ኋላ በትንሹ እስከ ሰባት ቤት አባቶቻችን እነማን እንደነበሩ፣ ተመዝግቦ ከተቀመጠው ስሞቻችውን በቃሌ ቆጥሬ እንድይዝ አስጠንተውኛል። ቁም-ነገሩ፣ በአፈ ታሪክ ሳይሆን፣ የሥነጽሑፍ ባህል ያዳበረ ሕብረተሰብ ነገሮችን በቅደም ተከተሉ፣ በጽሑፍ መዝግቦ መያዝ፣ የዕድገት ደረጃውን ያመለክታል። እስከነ ተረቱ፣ በአፍ የተነገረ ይረሳል፣ የተጻፈ ይወሳል ይባል የለ? በአፈ ታሪክ የሚወራው፣ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ስለማይገኝለት፣ ተረት ሁኖ ይቀራል። አንዳንዴም የጎደለውን ለማሸብረቅ ያልነበረው ገብቶበት ይቦካዋል።

በሴም በኩል፣ አንዷን ዘለላ መዘን እስክ አብርሃም ያለውን ትውልድ እንይ[iii]። ምክንያት አለን። ኖኅ ሴምን ወለደ፣ ሴም አርፍክስድን ወለደ። አርፍክስድ ሳላን ወለደ። ሳላ ኤቦርን ወልደ። ኤቦር ፋሌቅን ወለደ። ፋሌቅ ራግውን ወለደ። ራግው ሴሮሕን ወለደ። ሴሮሕ ናኮርን ወለደ። ናኮር ታራን ወለደ። ታራ አብርሃምን ወለደ። ይበቃል[1]። ከሴም እስክ አብርሀም 10 ትውልድ መሆኑን ልብ በሉልኝ።

አሁን ደሞ በሌላ በኩል፣ ከሴም ታናሽ ወንድም፣ ከካም እስከ ካህኑ አበመሌክ ያለውን የትውልድ የሐረግ ዘለላ መዘን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከተለያዩ ምንጮች እንመልከት።  

ኖኅ ካምን ወልደ። ካም ኩሽን ወለደ። ኩሽ ሳባን ወለደ፣ ሳባ ኑባን ወለደ። ኑባ አጋናን ወለደ። አጋና ኤታን ወለደ። ኤታን ናምሩድን ወለደ። ናምሩድ አዳማን ወለደ። አዳማ ራፌልብን ወለደ። ራፌልብን ቄናን ወለደ። ቄና መልክጸዴቅን ወለደ[iv]ከካም እስከመልከጸዴቅ 11 ትውልድ ነው። ኩሽ የት እንደቀረ አያችሁ? ከከነዓን ምድር እግሩም አልተቃነቀም

ኩሽ ናምሩድን ወለደ የሚል የተሳሳተ  ነገር አንብቤ፡ “ታላቁ ዶቦ ሊጥ ሆነ ብያለሁ።” ኩሽ ለናምሩድ ቅማንቱ[2] ነበር። አምስተኛ ትውልድ መሆኑ ነው። የነገሮች ውል ሲጠፋ እንዲህ መሳሳት ያመጣል። እንዲያው ዝም ነው። ምነው ኢትዮጵያውያንን ሊቃውንትን በጠየቁ!

ችግሩ ከየት እንደመጣ ላስረዳችሁ። ቫን ሰተር (Van Seter)[v] የተባለው ጸሐፊ እንደዘገበው ከሆነ፣ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ኦሪት ዘጸአት፣ ኦሪት ዘሌዋውያንና ኦሪት ዘኁልቁ የተጻፉት በ6ኛው እና በ5ኛው መቶ ዓመት ዓለም፣ ዕብራውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡ በኋላ ነበር። የራሳቸውን ታሪክ በአብዛኛው መዛግብቱ ቢኖራቸውም፣ በስደት ዘመን የካምን መዝገበ ታሪክ አልነበራቸውም። የናምሩድ ትውልድ ስሀተት ከዚህ ነው የተፈጠረው። እንዲህ ነው የሆነው። መጽሐፈ ኼኖክና፣ ሌሎች መጻፍትን፣ ኖኅ የሰጠው ለካም ነበር። ካም ደሞ ለታላቅ ልጁ፣ ለኩሽ ሰጠው። መጻፍቶቹ፣ ካህን ለሚሆኑት ለታላላቆቹ እየተወረሱ እስከ መልከጸዴክ ደረሱ። መልከጸዴቅ ለታላቅ ልጁ፣ ለኢትዮጵ (ሌላ ስሙ ኢትኤል) አወረሰው። ኢትዮጵ መጻሕፍቱን ይዞ፣ ዛሬ አፍሪካ ወደምትባለው መሬት ተሻገረ። እንዲህ እያለ ኢትዮጳውያን ሊቃውንት እጅ ገቡ። እስራኤላውያን፣ በዚያን ጊዜ የካምን ታሪክ የሚክታተሉበት መንገድ አልነበራቸውም። ታላቁን ናምሩድ የካም ዘር ቢሆንም፣ ውሉ ስለጠፋቸው የኩሽ ልጅ ብለውት አረፉ።

እነዚህን የሁለቱን የወንድማማቾችን ሐረጎች ምን አስመዘዘን? መክንያቱም የሴምና የካም 10ኛና 11ኛ ትውልድ በአንድ ጊዜ እንደኖሩና እንደሚገናኙም፣ ዝምድናቸውንም እንደሚያውቁ ለማመልከት ነው። መጽሕፍ ቅዱስ፣ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ምዕራፍ 14 ከቁጥር 17 እስክ 21 እንዲህ ይላል።

“ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመልሰ በኋላም፣ የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሊዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከጽዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ። እርሱም የእግዚአብሔር ካህን ነበረ። ባረከውም፦ አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚብሔር የተባረከ ነው። ጠላቶችህን በእጅህ ተጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብርሃምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።”

አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ተመራማሪዎች፣ ግዕዝን ለመማር የሚሟሟቱበት ምክንያት ብዙ የነገሮችን ግንኝነት ውል በፍጹም ሊያገኙት ባለመቻላቸው ነው ወደ ኢትዮጵያ የሚያንጋጥጡት። የአብርሃምንና የመልክጸዴቅን ግንኙነት (relationship) ጨርሶ ያልገባቸው፣ ፈረንጆች እንዲ ሲሉ ይናገራሉ።

Abraham encounters a mysterious figure named Melchizedek. So, who exactly is this mysterious Melchizedek? As Abraham is returning victorious from a risky battle, he passes by the city of Salem, and the king comes out to meet him. We're told that this king is also a priest who serves the same God as Abraham.[vi]

በቀላሉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡ አብርሃም ምስጢራዊ የሆነ መልከጸዴቅ የተባለ ሰው ያጋጥመዋል። እና፣ ይኸ ምስጢራዊ የሆነ ሰው ማነው? አብርሃም አደገኛ (risky) የሆነ ጦርነት ተዋግቶ ድል ነስቶ በሳሌም ከተማ ውስጥ ሲመለስ ይኸን የሳሌምን ንጉሥ ያገኘዋል። እንደነገሩን ከሆነ፣ ይኸ ንጉሥ፣ አብርሃም የሚያመልከውን እግዚአብሔር የሚያገለግል ካህን ነው። 

እንደዚህ ዓይነት ብዙ ነገሮች ከኢትዮጵያ ምንጮች ካልሆነ በስተቀር ሌላ ቦታ ድርና ማጉን ማገናኘት የማይቻሉ ነገሮች አሉ።[3]

እንግዲህ ዕውነተኛው ኩሽ የኖረው ወደ 5,000 ዓመተ ዓለም አካባቢ ነው። ወዲያው ከታላቁ ውሀ መጥለቅለቅ በኋላ ብዙ ህዝብ አልነበረም። የከነዓን ምድር ሁሉ ለኖኅ ልጆች የምትበቃ ሰፊ ነበርች። ኩሽ ከከነዓንም ምድር ወጥቶ አያውቅም። አፍሪካ የት እንዳለችም አያውቅም። ይኸ ጥቁር ህዝብን በደፈናው ነጮቹ ኩሽ የሚሉት ከግብጽ ተውሰው በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ጭብጥ የሌለው መላ ምት ነው። ቀላ ቀላ ባሉት ወራሪ ዘሮች ድቅልቅል ያሉት ግብጾች ወደደቡብ የገፏቸውን፣ ጥቆርቆር ያሉትን ኑቢያዎች የሰደቧቸው መስላኡቸው ኩሽ አሉቸው። የድንቁርና ጥግ ይሉሀል ይኸ ነው።

በ440 ዓመተ ዓለም ገደማ የኖረው ታላቁ የግሪክ የታሪክ ሰው፣ ሔሮዶቱስ (Herodotus) ስለኩሽ ሳይሆን ስለ አእትዮጵያ ("Αἰθιοπία - Aethiopia") ነበር እንዲህ እያለ የተርከው።

“... this country produces great quantities of gold, has an abundance of elephants and all the woodland trees, and ebony; and its men are the tallest, the most handsome, and the longest lived."[vii]

ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡ “አገሪቱ ብዙ ወርቅ የምታመርት፣ ብዙ ዝሆኖች የሚገኙባት፣ በጫካ የተከበበች፣ ብዙ ለአናጢ ሥራ የሚመቹ ግንዶች ያሏት፣ ህዝቧ በጣም ረጃጅም የሆኑ፣ በጣም የሚያማምሩ፣ እና በዙ ዓመታት መኖር የሚችሉ ናቸው” ይላል። ሔሮዶቱስ ማለት የዓለም ታሪክ አባት ተብሎ የተሰየመ ነው። የተቃጠለ ፊት የሚለው ትርክት ሰዎች እንደልማዳቸው የግሪክ ቃል ፈልገው አጠጋግተው ካልሆነ እንጂ፣ በሔሮዶቱስ ገለጻ አንድም ቦታ የተቃጠለ ፊት የሚል አናገኝም። ከየት ፈበረኩት? እንዲያው የተቃጠለ ፊት በግሪክኛ Kaméno Prósopo (Καμένο πρόσωπο) ነው። ምኑን ከምን አገናኙት?

ከ9ኛው እስከ 8ኛው ዓመተ ዓለም የኖረው ሆሜርም፣ ኤሊያድ ( Iliad)  በተባለው ድርሰቱ ሁለት ጊዜ፣ በኦዲሰይ (Odyssey) 3 ጊዜ ኢትዮጵያን በስሟ ጠርቶ ያሽሞነሙናታል። ግሪኮች በነበረው ስሟ፣ ኢትዮጵያ ብለው ጠሯት እንጂ፣ አዲስ ስም አላውጡላትም። ኢትዮጵያ ስለምትባለውና ስለህዝቧ ነው የተናገሩት። እነሱ ማን ናቸውና ነው ለኢትዮጵያ ስም የሚያወጡላት? በስሟ ጠርተው ነው ያደነቋት። የዘመኑ ታርክ አጥኚ ነን ባዮች እንዴት “የተቃጠለ ፊት” ሊሉት ቻሉ? እንዴት አጠጋጉት? ምናልባት፣ አዲግራትን “አዳ ጋራ” እንዳሉት አጠጋግተው ይሆን? ግሪኮች የሚያወሩት ስላጋጠመቻቸው “ኢትዮጵያ” ነበር እንጂ ስም አላወጡላትም። እነሱ በግልጽ ሲናገሩ የነበሩት፣ ስለ ኢትዮጵያን ልብ የሚሠርቅ ውበታቸው ነው እንጂ ስለተቃጠለው ፊታቸው አልንበረም። እስቲ ይታያችው፣ የግሪክ አፈታሪክ (mythology) ክዋክብትን በኢትዮጵያ ንግሥት ካሶፒያ (Cassiopeia) እና ንጉሥ ሲፊየስ (Cepheus) እያሉ ሲሰይሙ ስለተቃጠለው ፊት፣ ወይም ስለ ኩሽ እያወሩ ነበር? ስለ ልዕልቲቱ የካሶፒያና የሲፍየስ ልጅ፣ ስለ አንድሮሜዳ ሲያወሩ፣ ስለኩሽ ነበር ያወሩት? ከየት ነው ኩሽ መጥቶ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ የተደነቀረው? ኩሽ መጥፎ ስም ሁኖ ሳይሆን፣ የታሪክ መሠረት ስለሌለው ነው። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሉሀል ይኸ ነው። “ኢትዮጵያ” የሚለው መጠሪያ ስም ግን የተረጋገጠ የታሪክ መሠረት አለው። ለመሆኑ ይኽቺን ኩሽ የምትለዋን ቃል ማን ነበር መጀመሪያ አምጥቶ የደነቀራት? ከላይ እንደተገለጸው ግብጾች ነበሩ። ጢሞቲዎስ ኬንዳል (Timothy Kendal) የተባለ ሰው፣ እንዲህ ጉዱን ይነግረናል።

Kush, the Egyptian name for ancient Nubia, was the site of a highly advanced, ancient black African civilization that rivaled ancient Egypt in wealth, power and cultural development. The first capital of Kush lay at Kerma just south of the Third Cataract of the Nile.[viii]

“ኩሽ፡ ግምጾች፣ ለጥንታዊ ኑቢያውያን የሰጡት ስም ነው። አካባቢውም በጣም በሥልጣኔ የመጠቀና ከግብጽ ሥስልጣኔ፣ ሀብትና ኃያለነት ያላነሰ የጥቁር አፍሪካውያን አገር ነበር። የመጀመሪያው ዋና ከተማቸው ኬርማ ይባል ነበር። የሚገኛውም ከሦስተኛው የአባይ ካታራክት (ዓባይን እንደ የዓይን ሞራ የሸፈነ መሬት) ትንሽ ወደ ደቡብ ወረድ ብሎ ነው”። ግብጽን ከኢትዮጵ ዘሮች ከቀሟት በኋላ ማን ያልተፈራረቀባት አለ? ግሪክ፣ ሮማዎች፣ ቱርኮች፣ አረቦች ... ወዘተርፈ።

የአውሮፓ ቅኝ ግዥ ነጮች፣ ያቺን ከግብጽ ተዋሱና ትርጉሙን አጣመው ጥቁሩን ህዝብ በሙሉ ኩሽ አሉት። ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ስም ማውጣት አቅቷቸው ነው፣ ነጮቹ ግሪኮች አዲስ ስም የሚያወጡላቸው? ለነገሩ፣ አልተሳካላቸውም እንጂ፣ አቢሲናያስ ሊሉን ምን ያልፈነቀሉት ድንጋይ ነበር?

4)  ኢትዮጵያ - ምድረ ኢትዮጵ

የካምን ትውልድ ሀረግ ስንመዝ፣ 11ኛው ትውልድ ላይ ነበር የቆምነው። እሱም ካህኑ መልከጸዴቅ ነበር። ካህኑ መልክጸዴቅ ምሥጢራዊ ሰው ሳይሆን በቀጥታ ዘር ሐረጉ ሳይዛነፍ ከካም፣ የወረደ 11ኛ ትውልድ ነው። አብርሃምና መልከጸዴቅ ፈረንጆቹ distance cousin (የሩቅ የአጎት ልጆች) የሚሏቸው ናቸው።

መጽሐፈ ብሩክ ዣንሸዋ ቀዳማዊና ቀጥሎ ሰረገላ ታቦርን ስናነብ፣ ካህኑ መልከጸዴቅ ሦስት ወንዶችና አራት ሴቶች ልጆች እንደነበሩት እናገኛለን። ከሦስቱ ወንዶች፣ አንዱ ኢትኤል፣ በኋላ፣ ኢትዮጵዮ የተባለ የበኩር ልጁ እንዳለ እንገነዘበለን። በዚህን ጊዜ የከነዓን ምድር በሰው ተጨናንቃ ነበር። የሴም ልጆችም በዝተው ነበር። የካም ልጆችም እንደ የምድር አሸዋ በዝተው ነበር። በየጊዜው ለከብቶቻቸው ግጦሽና ውሀ፣ ለሚያርሱት መሬት፣ ከሴም፣ ከያፌትና ከወንድሞቻቸው ጋርም እየተጋፉ ይጣሉ ነበር። በዚህ የተነሳ፣ ኢትዮጵ ከብቶቹንና ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሲን (Sinai) በረሀ ወረደ ይለናል ሰረገላ ታቦር ገጽ 307። ከሲና ተንስቶ ወደ ደቡብ የዓባይን ወንዝ ተከትሎ እንደሰፈረ እንረዳለን። በዚህ መሠረት፣ ኢትዮጵ ግብጽን፣ ሱዳንን እና የዓባይ ምንጭ የሚፈልቅባትን መሬት የራሱ ርስት አድርጎ በራሱና በልጅ፣ በልጅልጆቹ ማንም ሳይጋፋው ማስተዳደር ቀጠለ። የያዛቸውም መሬቶች እንዳሉ የኢትዮጵ ምድር ወይም ግዛት እንደተባለ ጥንታዊ መዛግብት ላይ ተጽፏል። ሌላም ቦታ፣ የያፌትም ልጆቹ ሆኑ የሴም ልጆች በሄዱበት በራሳቸው አባቶች ስም የያዙትን መሬት መሰየም የተለመደ ነው። ለመሳሌ እንግላንድ የኢንተርኔት ምድር ናት። ስኮትላንድ፣ የስኮቲሾች ምድር ግዛት ናት። አየርላንድ፣ የአይሪሽች ምድር ናት። ምድርን ወይም ግዛትን አንዳንድ ቦታ በ..”ያ” (..ia) ተቀጽላ ይተኩታል። አረቢያ የአረብ ምድር ናት። ኢንዲያ የህንዶች የሚኖሩባት ምድር ናት። ዩጎስላቪያ፣ የዩግስላቮች አገር ነበርች። ራሺያ የሩስኪዎች አገር ናት። ሶማሊያ፣ የሶማሌዎች ምድር ናት። እንደዚሁም የኢትዮጵ ግዛት የነበረችው ጠቅላላ አህጉር ኢትዮጵያ ትባል ነበረ። ውቂያኖሷም፣ የኢትዮጵያ ውቂያኖስ ነበረ። 



በኋላ ላይ ግሪኮችም፣ ሮማውያንም፣ ሌሎችም ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵ ምድር ወረሯት። የአህጉሩንም ስም 17ኛ መቶ አጋማሽ ክፍለዘመን ላይ ሮማውያን “አፍሪካ” ብለው እንደሰየሟት ከተለያዩ ምንጮች እንረዳለን[ix] የጥንት ነባር ካርታዎችን ስናይ፣ የትም ቦታ ኢትዮጵያ የሚል እንጂ ኩሽ የሚል አገር አታገኙም። የሆኑ፣ የኋላ ታሪክ ተመራማሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች ናቸው ጥቁሮቹን አፍሪካውያንን ግብጽን ተከትለው “ኩሽ” ብለው ያረፉት። ከየት አመጡት? የኛዎቹ ጉዶች ያንን ይዘው ይንኮሻኮሻሉ። እግዚአብሔር ይማራቸው።

የሆነ ሁኖ፣ የኢትዮጵ 10 ትውልድ ዛሬ አፍሪካ የተባለችውን፣ የኢትዮጵን ምድር እስከዮቶር ድረስ ተራ በተራ እንዳስተዳደሯት እናገኛለን። ዮቶር ማለት፣ የሲጳራ አባት፣ የግብጻዊው ሙሴ አማት ነበር። ስማቸውን ስንዘረዝር፣ ኢትዮጵ አዜብን ይወልዳል። አዜብ ሞሪን ይወልዳል። ሞሪ ልብናን ይወልዳል። ልብናም መላክን ይወልዳል። መላክም ጋቢናን ይወልዳል። ጋቢናም አዲያምን ይወልዳል። አዲያምም ኖርኑስን ይወልዳል። ኖርኑስም ዮቶርን ይወልዳል። አንባቢን ላለማሰልቸት፣ እዚህ ላይ ቆም እንበልና ትውልዱ፣ እያለ እስከ ንጉሥ አክሱም ይኸዳል። አክሱም ማለት፣ የኛ ዘመናዮች ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ፣ “አካሱማ” ከሚለው የኦሮሚኛ ቋንቋ የመጣ ሳይሆን፣ ነግሥተ ሳባ የተባለችው ንግሥት አያት ነበር። አክሱምን አካሱማ ያሉን “ሁንዱማ ኬኛዎች” ነገ ሚኒስቶታ የተባለ የአሚሪካ ከተማ ውስጥ እየበዙ መጥቷልና፣ “ማና ሶታ” ነበር እንዳይሉን፣ ምን ይገድባቸዋል?

ስለዚህ ኩሽ ብሎ ነገር አፍሪካ ውስጥ አልነበረም። ባይሆን እንኳን የካም ልጆች ነን ቢሉ ያምርባቸዋል። ከሴምና ከያፌት እኩል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ነዋ። የሴም ልጆች ሴማውያን ናቸው። የያፌት ልጆች እነ ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ይልሳ፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣  ቴራስና የልጅ ልጆቻቸው በሙሉ ያፌታውያን ነው የሚባሉት። የካም ልጆች ካማውያን (Hamites) እንዳይባሉ ጥራዝ ነጠቅ የኦሮሞ ልሂቃን ያንኮሻኮሹት ምን ተአምር ተፈጥሮ ነው? ምን ለመደበቅ ታስቦ ነው ከጊዜ በኋላ ኩሽ የተባሉበት ምክንያት?

ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን ማን ነን? የሚቀጥለው ክፍል ያብራራዋል።

5)   ማጠቃለያ - እኛ ማን ነን?

እኛማ ዓለም ያወቀን ጸሐይ የሞቀን ከጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ስንቀነስ፣ ስንቆረጥ የተረፍን፣ የአባታችንን፣ የኢትዮጵን ስም ወርስን የቀረን ኢትዮጵያውያን ነን። እየቆረሱን አናልቅ ብለን ያስቸገርናቸው ህዝብና አገር ነን። አጼ ዘርዓ ያቆብ እንኳን 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዛሬው በእጅጉ የሰፋች አገርን ሲያስተዳድሯት ነበር። ትላንት፣ ዓይናችን እያየ ጂቡቲና ኤርትራ ሌላ አገር ሁነዋል። ዛሬ፣ ዘረኞች 83 ቦታ በቋንቋ ሸንሽነውን፣ የፈለገ መገንጠል ይችላል የሚል “ሕገ መንግሥት” ቀርጸው፣ ሊለያዩንና የኢትዮጵያን ስም ከምድረ ገጽ አጥፍተው በኩሽ ሊቀይሩ ሲታትሩ እናያለን። በተለይ ኩሽ ኩሽ እያሉ የሚጮኹ የኦሮሞ ልሂቃን በሚያስፍር ሁኔታ ህዝቡን በሴምና በኩሽ ከፍለው ደም ለማፋሰስ ሌት ተቀን ይጥራሉ። ነገሩ፣ ጸረ ሴማዊነት (antisemitic)(x) ፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑ ቢጠቁምንም፣ ቦታውን የሳተ ነው። እዚህ ሴማውያን የሉም። እስራኤልና፣ አንዳንድ የተሰደዱብት አገር ነው የሚኖሩት። እዚህ የነበሩትም ሂደዋል። "ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ" ይሉሀል ይኸ ነው።

ኩሽ ኩሽ ባዮችን እረፉ እንላለን! አታንኮሻኩሹብን! ኩሽ ብሎ ነገር የለም። ካምና ሴም የሚባል የተከፈለ ህዝብ የለንም። የዘመናችን ታልቁ የቤተክርስቲያናችን በሕይወት የሚገኙ ሊቅ፣ አባታችን ቀሲስ አስተራዬ ጽጌ፣ “ሕብረ ሐመልሚል” በሚል ርዕስ “የአቶ መላኩ አስፋ የሕይወት” በሚል ርዕስ በሚያዝያ 1 ቀን 2006  ዓ.ም. ባበረከቱት ጽሑፍ እንዲህ ብለው ነበር።

የመላኩ ሰውነት   አርአያ ኮሰኮስ ዘብሩር የተባለውን  የሁላችንን ሰውነት  የምንመለከትበት መስተዋታችን ነው።   በሌላ  አገላለጽኢትዮጵያዊነታችን በለመለመ መስክ በቅለው፤ አብበው፤  በሩቅ የሚታዩ  የጽጌ ረዳ፤ የአደይ አበባ፤ የሶሪት አበባ፤ የሱፍ አበባ መሳይ ይህ ቀረሽ የማይባል የውበት ውጥንቅጥ ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ፤ ወፍ ዘራሽነትህን ተቀብለህ ቦታህን ፈልግ ሊባል ይገባዋልእያሉ ሊቃውንት አበው አስተምረውናል።

ይኸ አባባል ዝም ብሎ ነገር ለማሳመር የተነገረ፣ ሳይሆን ሀቅ ላይ ተመሥርቶ የተነገረን፣ ዕውንተን ያዘለ ጥልቅ መልዕክት ነበር። ምሑራዊ ትንተና ነው። አባታችንን “ቃለ ሕይወት ያሰማልን” እያልኩ፣ ወደሌላው የመጨረሻ የኩሽ ትርክት የቀብር ሳጥን ላይ የሚመታ 12 ቁጥር ሚስማር ልለፍ። ይኸውም ኩሽ ወይም ሴም የምባል ዘር አለመኖሩን የሚነግረን ሳይናስዊ ቀመር ነው። አረቦች ሐባሽ ያሉን ምክንያት ነበራቸው።

በአገራችን፣ ጥርት ያለ ኩሽ የለም፣ ሴምም የለም ስንል በታሪክ በሳይንሱም ላይ ተመርኩዘን ነው። ኢትዮጵያዊያን ነን። የምንናገረው ቁንቋ፣ የማን ልጆች መሆናችንን፣ ማንነታችንን ሊያሳየን አይችልም። ቋንቋ የሕብረሰብ መግባቢያ እንጂ፣ የዘር ሀረግ መምዘዢያ አይደለም። ዕረፉ አትንኩሻኮሹብን! በታሪካችን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ20ኛው መቶ መጨረሻ ክፍለ ዘመንና በ21ኛ መቶ መጀመሪያ ኢትይጵያውያን በዓለም በስደት እንደጉድ ተዘርተናል። ልጆቻችን እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስዊዲሽኛ፣ ኖርዊይጅኛ፣ ጀርመኒኛ፣ ግሪክኛ ጣሊያንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ... ወላጆቻቸው እንደተሰደዱብት አገር አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አድርገው ያድጉበታል። ታዲያ ያ አይደለም ማንነታቸውን የሚውስነው። ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ሲሰደዱ፣ ኢትዮጵያን በልባቸው ይዘው ነው በዓለም የተዘሩት። በሂዱበት፣ የራሳቸውን ባህልና አኗኗር ይዘው ነው የሚንከራተቱት። እንዲያውም፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚብስባቸው፣ አገራቸው እየኖሩ ሳይሆን ከአገር ሲወጡ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ምግባቸው እንኳን በተቻለ መጠን አትለውጥም። የኢትዮጵያ በረበሬ ጣዕም ሌላ ቦታ የለችም። ምጥን ሽሮአቸው እንኳን አትለያቸውም። በሔዱብት ሬስቶራንታቸው፣ ትከተላቸዋለች። በዓላቶቻቸውን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ነው የሚያክበሩት። ቤተ ዕምነታቸውም፣ አብራቸው ተሰዳለች። ልጆቻቸውንም፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለማሳደግ ነው የሚጥሩት። ሕጻናቱ፣ ኢንደሌላው ሕብረተሰብ፣ የማንነት ጥያቄ (identity crisis) ጭንቀት አይታይባቸውም። በኩራት ኢትዮጵያዊነታቸውን ይናገራሉ። ኤርሚያስ በትንቢቱ (13:23) በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ወይስ ነበር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ይችላልን?” ያለበት ምክንያት ነበረው። ቂሲስ አስተራየን የሚሉትም ይኸንኑ ውበት ነው። አንድ የሚያደርግን፣ በውስጣችን የሚዘዋወረው የደማችን አንድነት ነው እንጂ፣ የምንናገረው 83 ቋንቋዎች አይደለም።

እስቲ አንድ ከዚህ በታች የአለውን የዘረመል (DNA) ምርመራ ውጤት ከልብ ተመልክቱ። ወደ ሌላ አትዩ! አትኩራችሁ ተመልከቱ፡ አጥኑ! አገናዝቡ! ምን ይታያችኋል?



አንድ ንጹህ ኦሮሞ ፈልጋችሁ አታገኙም። አንድ ንጽህ አማራም ፈልጋችሁ አታግኙም። ኩሽ እየተባለ የሚንኮሻኮሽበት ኦሮሞ የኦሮሞ ልሂቅ፣ ከአማራው፣ ከአፋሩ፣ ከትግሬው፣ ከወላይታው ተደባልቋል። ለመድኃኒት እንኳን ንጹህ ኦሮሞ አይገኝም። እምኑ ጋ ነው ኩሽነቱ? እንድገመው! ቋንቋው? ቋንቋንማ ማንም ሊናገረው ይችላል። ስንት ኦሮሚያ ውስጥ የተወለዱ አማሮች ተብለው የተፈረጁ ኦሮሚኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው እንደሆነ እነዚህ የተማሩ መሀይማን ይረዱ ይሆን?

አማራውም ቢሆን፣ ከኦሮሞው፣ ከአፋሩ፣ ከትግሬው፣ ተደበላልቋል። ደሙ ሲመረመር አንድ ንጹህ አማራ በአጉሊ መነጽርም (microscope) ተፈልጎ አይገኝም። እምኑ ጋ ነው ሴማዊነቱ? ቋንቋውን ስለተናገረ? እንዳልነው ቋንቋማ መግባቢያ ነው። ስንቱ አማራ ያልሆነ ይራቀቅበታል።

እናንተ የተማራችሁ መሀይማን! ኩሽ አገራችንን ረግጦም አያውቅም። የኖረው ክ7023 ዓመት በፊት በከነዓን ምድር ነው። ወደዚህ የመጣው ከኩሽ 12ኛው ትውልድ ኢትዮጵና ቤተሰቡ ነበሩ። በዝተው ተባዝተው አህጉሯን ስለሞሏት ግዛቱም ኢትዮጵያ ይባል ነበር። ኢትዮጵያ በታሪኳ ስደተኞችን ስትቀበል የኖረች ናት። በተለያየ መንገድ በአረቢያም ይሁን በሱዳን በኩል በተለያየ ጊዜ የሴም ልጆች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም ከካም ልጆች ጋር ተጋብተው ተዋልደው ቀሲስ አስተራየ እንዳሉት “ህብረ ሐመልሚል” ፈጥረዋል። የተለየ ሴም ወይም ኩሽ የምትሉት ነገር የለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። አትንኮሻኮሹብን።

ትላንት ያልነበራችሁትን፣ ዛሬም ያልሆናችሁትን፣ ነገም ልትሆኑ የማትችሉትን ኩሽ እያላችሁ አታንኮሻኩሽብን! በሀሰት ተርክት ህዝባችንን አታምሱት። ስላም ስጡን።

አበቃሁ።




End Note - የመጨረሻ ግርጌ ማስታውሻ


[1] ከሴም እስከ አብርሀም ያለው ትውልድ በደረገጹ ላይ ክ10ኛው ተራ ቁጥር ጀምሮ ተደርድሯል። የተወሰደውም፣ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ነው።

[2] ትውልድ ሲተነተን እንዲህ ነው፡ ልጅ አባት አያት ቅድመ-አያት ቅም-አያት ቅማንት፣ ሽማት ፣ምንዥላት አንጅላት፣ ፍናጅ፣ ቅናጅ ፣አስልጥ አምስጥ ማንትቤ፣ ደርባቴ

[3] ለምሳሌ፤ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ቁጥር 18 ላይ “እርሱም ፦ ወደ ከተማ እገሌ ዘንድ ሂዳችሁ ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ተቃርባል። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት።” ማነው እገሌ? መልሱን ከሐሙሱ ሰይፈ ሥላሴ፣ ተአምሩ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ከአሪዮስ ጋር በኒቅያ ጉባኤ ሲከራከሩ፣ በቁጥር 18 ላይ፣ ይኽ እገሌ፣ ወዳጁ አልዓዛር መሆኑን እንረዳለን።



[ii] Baum, James E.: Savage Abyssinia, J.H Sears & Company, Inc. Publishers, New York, 1928, P. XVii

[iv] መጽሐፈ ብሩክ፣ ዣንሸዋ ቀዳማዊ ገጽ 269 እና ሰረገላ ታቦር ገጽ 290 (ትርጉም፣ መሪ ራስ በላይ አማን)።

[v] Van Seters, John (2004). The Pentateuch: A Social-science Commentary. Continuum International Publishing Group. ISBN 978-0567080882

[vii] https://stockton.edu/hellenic-studies/documents/chs-summaries/kantzios96.pd

[viii]f

[viii]https://www.pbs.org/wonders/Episodes/Epi1/1_wondr2.htm#:~:text=Kush%2C%20the%20Egyptian%20name%20for,Third%20Cataract%20of%20the%20Nile.

[ix] https://youtube.com/shorts/kdMNA-szyKk?feature=share

x Girma Berhanu: The New Frontier Of Antisemitism: Racial Discourse And Oromo Extremism In Ethiopia – Analysis, https://www.eurasiareview.com/29062023-the-new-frontier-of-antisemitism-racial-discourse-and-oromo-extremism-in-ethiopia-analysis/?fbclid=IwAR2qRe-3GyGWSQgqMLmaeKkaFJLltxbr7LTFOEkDiqO5m5GNtMDHcFZ_RTc